Back to Top
የተከበሩ ሸይኽ! ትክክለኛው እና ተቀባይነት የሌለው የተወሱል አይነት ምንና ምን ናቸው?
   ዐቂዳ (እምነት ነክ ጉዳዮች)        ምልጃ

ትክክለኛው ተወሱል እና ተቀባይነት የሌለው የተወሱል ዓይነት


ጥያቄ(56): የተከበሩ ሸይኽ! ትክክለኛው እና ተቀባይነት የሌለው የተወሱል አይነት ምንና ምን ናቸው?
መልስ:

ተወሱል ማለት “ተወሰለ” “የተወሰሉ” ማለትም ተዳረሰ መዳረስ ከሚለው የዓረብኛ ስረወ ቃል የመነጨ ነው። ወደ ሚያልመው አላማ እና ግብ ሊያዳርሰው የሚችል መዳረሻ ሰበብ ሲይዝ “ተወሰለ”ተዳረሰ መዳረስን ይባላል። የዚህ ቃል መነሻው ወደሚፈለግ ግብ ለመድረስ መፈለግ ወይም መከጀል የሚል ነው። ተወሱል ሲባል ለሁለትም ይከፈላል።

አንደኛው ትክክለኛው የተወሱል ክፍል: ወደሚፈለገው ግብ በትክክለኛ መዳረሻ መዳረስ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ: ወደ ተፈላጊው ግብ የማያዳርስ የመዳረሻ አይነት ነው።

የመጀመሪያው የተወሱል አይነት ማለትም ፡ ወደ ሚፈለገው ግብ በትክክለኛ መዳረሻ መዳረስ የሚለው፦

ብዙ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነሱም ውስጥ በአላህ መልካም ስሞቹ እና ባህሪያቶቹ ተወሱል ማድረግ ሲሆን በጥቅሉ ወይም በተለየ መልኩም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ በጥቅሉ በአላህ መልካም ስሞቹ እና ባህሪያቶቹ ተወሱል ማድረግ ለሚለው፦ ከዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ ተዘግቦ እንደመጣው ፦ “አላህ ሆይ! እኔ ባሪያህ፣የወንድ ባሪያህም፣የሴት ባሪያህም ልጅ ነኝ። ሁለ ነገሬ በእጅህ ነው። ውሳኔህ በኔ ላይ ተፈፃሚ ብይንህ ፍትሓዊ ነው።ቁርኣንን ለኔ ቀልብ ማርጠቢያ ታደርግልኝ ዘንድ በስሞችህ ሁሉ እማፀንሃለሁ። አንተ ራስህን በጠራህባቸው ወይም ቁርኣንህ ውስጥ ባሰፈርካቸው፣ከፍጡራንህ ለአንዱ ባስተማርካቸው ወይምለማንም ሳትገልፅ አንተ ዘንድ ባስቀረከውም ስሞችህ እማጸነሃለው።” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ) ”በስሞችህ ሁሉ እማፀንሃለሁ።” ከሚለው አ/ነገር በመነሳት እዚህ ቦታ ላይ  በአላህ ስሞችና ባህሪያቶች ተወሱል  በጥቅሉ ነው የተጠቀሰው።

በተለየ መልኩ የሚለው ደግሞ (ከሐጃው) ከጉዳዩ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችልን ከአላህ ስሞች መካከል አንዱን ለይቶ በመጥራት አላህን መማፀን ነው። ለምሳሌ፦ ከአቡበከር ተዘግቦ በመጣው ሐዲስ ላይ መልዕክተኛውን ሰላት ላይ ሲሆኑ የሚያደርጉትን ዱዓ በጠየቋቸው ጊዜ እንዲህ ብለዋቸዋል፦

“አላህ ሆይ! እኔ ነፍሴን በርካታ በደሎችን በድያለሁ። ወንጀልን ከአንተ ውጭ የሚሸፍን(የሚምር) የለም። ከአንተ  የሆነን ምህረት ለግሰኝ። እዘንልኝም። አንተ መሓሪና አዛኝ ነህና።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
በነዚህ ሁለት ስሞች(አል ገፉር እና አር ረሒም) አላህን ምህረትና እዝነት መጠየቅ ከጉዳዩ ጋር አብሮ የሚገጥሙ ስያሜዎች ናቸው። ይህ አይነቱ የተወሱል አይነት ቀጣዩ የቁርኣን ትዕዛዝ ውስጥ የሚካተት ነው።”
ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፡፡ (ዱዓ ስታደርጉ) በእርሷም ጥሩት፡፡” [አል አዕራፍ ፡180]

   እዚህ ቦታ ላይ ዱዓ(ጥሪ) ሲባል ዱዓኡ መስኣላና ዱዓኡ ዒባዳ ይካተታሉ። በባህሪያቶቹ ተወሱል ማድረግ የሚለው ደግሞ ልክ እንደ ስሞቹ ጥቅልና ለየት ያሉ የተወሱል አይነት አላቸው። ጥቅል በሆኑ በአላህ መገለጫ ባህሪያቶች ተወሱል ማድረግ ለሚለው ፦ አላህ ሆይ! መልካምና ውብ በሆኑ ስሞችህ እና ከፍና ላቅ ባሉ ስሞችህ እማፀንሃለሁ። የሚለው በምሳሌነት ተጠቃሽ ነው። ለየት ባሉ በአላህ መገለጫ ባህሪያቶች ተወሱል ማድረግ ለሚለው ደግሞ ፦ ሐዲስ ላይ እንደመጣው ፦ “አላህ ሆይ! በሩቅ ሚስጥር እውቀትህና በፍጡራን ላይ ባለህ ችሎታ እማፀንሃለሁ። መኖሬ ለኔ መልካም መሆኑን ካወቅክ በህይወት አቆየኝ።ሞት ለኔ መልካም እንደሆነ ካወቅክ ደግሞ ለህልፈት አብቃኝ።” “በሩቅ ሚስጥር እውቀትህና በፍጡራን ላይ ባለህ ችሎታ እማፀንሃለሁ።” እዚህ  ላይ ደግሞ ዒልም (ዕውቀት) እና ቁድራ (ችሎታ) በሚባሉት መገለጫ ባህሪያቶች ወደ አላህ ተወሱል ተደርጓል። ይህ አንደኛው የተወሱል አይነት ነው።

ሁለተኛው የተወሱል አይነት ደግሞ፦ አንድ ሰው በአላህ ማመን እና በመልክተኛው መልዕክተኝነት ማመን በሚባለው መልካም ስራ ወደ አላህ ተወሱል ማድረጉ ሲሆን ለምሳሌ ፦ “አላህ ሆይ በአንተ አምላክነት በመልዕክተኛው መልክተኝነት አምኛለሁና ወንጀሌን ማረኝ፣ለመልካሙ ሁሉ ግጠመኝ።”ሊል ይችላል። ወይም አላህ ሆይ! በአንተ በማመኔ መልክተኛውን በመቀበሌ እንዲህ እንዲህ  ያሉ ነገሮችን …  እጠይቅሃለሁ።” ሊል ይችላል።ከዚህም የተወሱል አይነት ከሚካተተው የሚከተለው የቁርኣን መልክት ይገኝበታል፦ “ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀንንም በመተካካት ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ፡፡ (እነርሱም) እነዚያ ቆመው፣ ተቀምጠውም፣ በጎኖቻቸው ተጋድመውም አላህን የሚያወሱ በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ፡-

«ጌታችን ሆይ! ይኸን በከንቱ አልፈጠርከውም፤ ጥራት ይገባህ፤ ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን» የሚሉ ናቸው፡፡” [አልዒምራን:190_ 191] እንዲሁም እስከ [አል ዒምራን 193 ] ያለው
«ጌታችን ሆይ! እኛ በጌታችሁ እመኑ በማለት ወደ እምነት የሚጠራን ጠሪ ሰማን፡፡ አመንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ኃጢአቶቻችንንም ለኛ ማር፡፡ ክፉ ሥራዎቻችንንም ከኛ አብስ፡፡ ከንጹሖቹም ሰዎች ጋር ግደለን፤»

ስለሆነም በነዚህ አንቀፆች መሰረት አማኞች በአላህ በማመናቸው ወንጀላቸውን እንዲምርላቸው ሐጢያቶቻቸውንም እንዲያብስላቸውና ከአብራሮች (መልካም ሰሪዎች) ጋር እንዲገድላቸው ወደእሱ ተወሱል አድርገዋል።

ሦስተኛው የተወሱል ዓይነት፦ በመልካምና በሰናይ ምግባራት ተወሱል ማድረግ ሲሆን ከዚህ የተወሱል ዓይነት ማስረጃ (ምሳሌ) ሆኖ የሚቀርበው ሦስቱ በጉዞ ላይ ሳሉ ዝናብ ገጥሟቸው በመሸሽ ወደ ዋሻ የተጠለሉት ሰዎች ታሪክ ነው። እርሱም(ታሪካቸውም)፦ ዋሻው ውስጥ ሲጠለሉ ማንቀሳቀስ የማይችሉት ትልቅ ቋጥኝ ተንከባሎ የዋሻውን በር ዘጋባቸው። ሦስታቸውም ለአላህ ሲሉ በሰሯቸው መልካም ስራ ተወሱል አደረጉ።ከእነሱ ውስጥ አንዱ ለእናቱ መልካም በመዋሉ፣ሁለተኛው ደግሞ በተሟላው ጥብቅነቱ ሦስተኛው ደግሞ ለቅጥረኛው አማናውን ጠብቆለት ተገቢውን ደሞዝ ሳይቀንስ በመስጠቱ ተወሱል አደረጉ። ሁላቸውም ፦ “አላህ ሆይ! ይህንን ስራ ለአንተ ስንል ካደረግነው አሁን ካለንበት ጭንቀት ገላግለን።” በማለት አላህን ተማፀኑት። ቋጥኙም ተንከባሎ በሩን ክፍት አደረገላቸው።” ይህ በመልካም ስራ ወደ አላህ ተወሱል ማድረግ ውስጥ የሚካተት  ነው።

አራተኛው የተወሱል ዓይነት፦ ተወሱል የሚያደርገው ግለሰብ እርሱ ያለበት ሁኔታ እና የአላህ እገዛ ለሱ በጣም እንደሚያስፈልገው በማስተዛዘን ተወሱል(ዱዓ) ማድረግ ነው።

ከዚህ የተወሱል ዓይነት የሚጠቀሰው ሙሳ ዓለይሂ ሰላም ያደረገው ዱዓ ነው፦

«ጌታዬ ሆይ! እኔ ከመልካም ነገር ወደኔ ለምታወርደው ፈላጊ(ከጃይ) ነኝ» አለ፡፡” [አልቀሰስ:24]

ሙሳ ይህን በሚልበት ግዜ የአላህ መልካም ነገር ለርሱ ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ ተወሱል አድርጓል።

ከዚሁ የተወሱል አይነት የሚመደበው ዘከሪያ (ዓለይሂ ሰላም) ያደረገው ተወሱል(ዱዓ) ይገኝበታል።

«ጌታዬ ሆይ! እኔ አጥንቴ ደከመ፤ ራሴም በሺበት ተንቀለቀለ፤ አንተም በመለመኔ ጌታዬ ሆይ! (ምንጊዜም) ዕድለ ቢስ አልሆንኩም፡፡” [መርየም:4]

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የተወሱል ዓይነቶች ሁሉም ይፈቀዳሉ፤ ምክንያቱም በነሱ ተወሱል በማድረግ የሚፈለገውን ዓላማ ለማግኘት ትክክለኛ ሰበቦች እና ጥረቶች ናቸው።


 




Share

ወቅታዊ