Back to Top
የሰላት መስፈርቶች ምን ምን ናቸው? እንነሱ ሳይሟሉ ቢቀር ሰላት ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖስ ምንድ ነው?

ጥያቄ(89): የሰላት መስፈርቶች ምን ምን ናቸው? እንነሱ ሳይሟሉ ቢቀር ሰላት ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖስ ምንድ ነው?
መልስ:

የሰላት መስፈርቶች ማለት የሰላት ትክክለኝነት በርሱ ላይ የተንጠለጠለ ማለት ነው።

ሸርጥ ማለት በአረብኛው ምልክት ማለት ነው። ልክ አላህ በቁርኣኑ እንዳለው ፤ “ሰዓቲቱንም ድንገት የምትመጣባቸው መኾንዋን እንጅ ይጠባበቃሉን? ምልክቶችዋም በእርግጥ መጥተዋል፡፡ “ [ሙሀመድ:18]

በኡሱሊዮች ኢስጢላሕ (ቴክኒካዊ ፍቺ) ደግሞ ሸርጥ ማለት፤ መስፈርት የተደረገው ነገር ከሌለ መስፈርት የተደረገለትም ነገር የለም፤መስፈርት የተደረገው ነገር መኖር መስፈርት የተደረገለት ነገር አለ ማለትን አያሲዝም።

የሰላት ሸርጦች ብዙ ሲሆኑ ከነዚያ መካከል ዋናዋቹ የሚከተሉት ናቸው፤ ወቅትን ጠብቆ መስገድ አላህ አዘወጀለ እንዳለው ፦

“ሶላት በምእምናን ላይ በጊዜያት  የተወሰነች ግዴታ ናትና፡፡” [አኒሳእ፡103]

ለዚህም ሲባል ብዙ በጊዜ የተገደቡ ግዴታዎች ጊዜያቸው ካልደረሰ ግዴታነታቸው አይፀድቅም። አንድ ሙስሊም ሰላቱን ሲሰግድ ወቅቱን ጠብቆ  መስገድ በርሱ ላይ ግዴታ ይሆናል። የሰላት ወቅቶች አላህ አዘወጀለ በቁርኣኑ በጥቅል የጠቀሳቸው ሲሆን መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ደግሞ በሐዲሳቸው በዝርዝር ጠቅሰውታል።

የሰላት ወቅትን አስመልክቶ በቁርኣን ላይ አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላል፦

“ሶላትን ከፀሐይ መዘንበል እስከ ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ፡ የፈጅርም ሶላት ስገድ፡፡ የፈጅር ሶላት (መላእክት) የሚጣዱት ነውና፡፡” [አል ኢስራእ ፡78]

እስከ “ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ፡” ማለት እስከ እኩለ ለሊት ስገድ ማለት ነው። ፀሐይ ከተዘነበለችበት ሰዓት አንስቶ  እስከ  እኩለ  ለለሊት ያሉት አራት ሰላቶችን ያካትታል። እነሱም ፦ ዙህር፣ዐስር፣ መግርብ እና ዒሻ ናቸው። እነዚህ ሰላቶች ያለምንም ጣልቃ በተከታታይ የሚመጡ ሰላቶች ናቸው። የዙህር ወቅት ፀሐይ ከአናት ዘንበል ካለችበት ሰዓት አንስቶ የማንኛውም ጥላ የራሱን ያክል እስኪሆን ያለው ሰዓት ነው። የዐስር ወቅት ደግሞ፤ ከዚህ ማለትም የማንኛውም ጥላ የራሱን ያክል ከሆነበት ሰዓት አንስቶ ፀሀይ ቢጫ እስክትሆን ድረስ ነው። የመግሪብ ወቅት ደግሞ፤ ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ ቀዩ አድማስ እስኪጠልቅ ያለው ሰዓት ነው። የኢሻ ወቅቱ ደግሞ ቀዩ አድማስ ከጠለቀበት ሰዓት አንስቶ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ይቆያል። እነዚህ ሰላቶች አንዱ ከሌላው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው። ከእኩለ ለሊት ጀምሮ ፈጅር እስኪወጣ ያለው ጊዜ የግዴታ ሰላቶች ወቅት አይደለም። የፈጅር ሰላት ወቅት ደግሞ ጎህ ከቀደደበት ሰዓት አንስቶ ፀሐይ እስክትወጣ ያለው ጊዜ ነው። ለዚህም ሲባል የፈጅርን ወቅት አላህ አዘወጀለ ከሌሎች ሰላት ለይቶ ጠቅሶታል። “ሶላትን ከፀሐይ መዘንበል እስከ ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ።” ካለ በኋላ ” የፈጅርም ሶላት ስገድ፡፡ የፈጅር ሶላት (መላእክት) የሚጣዱት ነውና፡፡” አለ። ስለዚህም ከላይ ባሳለፍነው መሰረት የሰላት ወቅቶችን በዝርዝር ሐዲስ ላይ ተጠቅሰው መጥተዋል ማለት ነው።።

እነዚህ ወቅቶችን አላህ አዘወጀለ በባሮች ላይ ግዴታ አድርጓቸዋልና አንድ ሙስሊም ሰላት ወቅቱ ከመገባቱ አስቀድሞም ሆነ አሳልፎ ሊሰግድ አይገባም። ሰላቱ ተክቢረተል ኢህራም የሚባልበት ሰኮንዶች ያህል ቀርቶት እንኳ ሰላትን ቢሰግድ ተቀባይነት አይኖረውም። ምክንያቱም ሰላት በወቅቱ መስገድ ግዴታ ነውና። ሸሪዓዊ ዑዝር ኖሮት ለምሳሌ ተኝቶ አሊያም ረስቶ ሰላትን ከወቅቷ ያዘገየ ከሆነ ዑዝሩ ሲወገድለት ሰላቱን ይሰግዳል። የአላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ስላሉ፦

 “ሰላት የረሳ ወይንም ሳይሰግድ በእንቅልፍ ያሳለፈ ሲያስታውስ ወይንም ሲነቃ ይስገድ። ማበሻው ይሄ ብቻ ነው።” ካሉ በኋላ ቀጣዩን አንቀፅ አነበቡ፦

“ሶላትንም (በእርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ፡፡” [ጧሃ፡14]

ሸርዓዊ ዑዝር ሳይኖረው ግን ሰላትን አዘግይቶ የሚሰግድ ለምን አንድ ሺ ሰላት አይሰግድም! ሰላቱ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም አንድ  ሰው በወቅቱ መስገድ ሲኖርበት አዘግይቶ ቢሰግድ ሰላቱ ምንም አይጠቅመውም። ያለ ዑዝር አዘግይቶ ብዙ ጊዜ ቢሰግድም እንደሰገደ አይቆጠርም። ለዚህም ማስረጃው የመልክተኛው ንግግር ነው፦

 “የእኛ  ትዕዛዝ የሌለበት ስራ የሰራ ስራው በርሱ ላይ ተመላሽ ነው።”

ሰላትን ወቅቱ እስኪወጣ ጠብቆ  የሰገደ  አላህና መልክተኛው ካዘዙት ውጭ ሰግዷልና በርሱ ላይ ተመላሽ ይሆንበታል።

ሆኖም አላህ አዘወጀለ በባሮች ላይ በማዘኑ የተነሳ ሰላትን በወቅቱ መስገድ ላልቻሉ ሰዎች ሰፊ እድል ሰጥቷቸዋል። ስለሆነም ዙህርና ዐስርን እንዲሁም መግሪብና ዒሻን አንድ ላይ ሰብስቦ መስገድ ይቻላል። አንድ ሰው ሰላትን በወቅቱ መስገድ የሚከብደው ከሆነ ሁለት ሰላቶችን ሰብስቦ በማስቀደም አሊያም በማዘግየት በአንዱ ወቅት ላይ እንደገራለት መስገድ ይፈቀድለታል። አላህ አዘወጀለ እንዲህ ይላልና ፦

“አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፡፡ በእናንተም ችግሩን አይሻም፡፡” [አልበቀራ፡185]

 ሙስሊም ዐብዱላሂ ኢብኑ ዐባስ ጠቅሰው በዘገቡት ሐዲስ የአላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም መዲና ውስጥ ሳሉ ያለ ስጋት፣ ዝናብ ሳይዘንብ ዙህርና ዐስር እንዲሁም መግሪብና ዒሻን ሰብሰበው ሰግደዋል። መልክተኛው ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም  ይህን ለምን እንዳደረጉ ሰሓቢዩ ኢብኑ ዐባስ በተጠየቁበት ጊዜ ፦

 “ዑመቶቹን ላለማስቸገር።” በማለት መለሱ።

ከዚህ የምንረዳው አንድ ሰው ከተቸገረ ሁለት ሰላቶችን ሰብስቦ  በአንዱ ወቅት መስገድ ይችላል የሚለው ነው፤ ማለትም ዙህርና ዐስርን አሊያም መግሪብና ዒሻ ሰብስቦ መስገድ ይፈቀድለታል።

የሰላት ወቅት ከሰላት ሸርጦች መካከል እጅግ ወሳኝ ስለሆነ ሰላትን ለመስገድ ሸርጥ እና ሰበብ ሆኗል።

ከሰላት መስፈርቶች መካከል በተጨማሪም ሀፍረትን መሸፈን ይገኝበታል። አላህ አዘወጀለ እንዲህ ብሏልና፦

 ”የአዳም ልጆች ሆይ! (ኀፍረተ ገላችሁን የሚሸፍኑትን) ጌጦቻችሁን በመስገጃው ሁሉ ዘንድ ያዙ፡፡ ብሉም፤ ጠጡም፤ አታባክኑም፡፡” [አል አዕራፍ፡31]

 የአላህ መልክተኛ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም ለጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ እንዲህ ብለውታል፦

“ልብሱ ሰፊ ከሆነ ተጠቅለልበት ጠባብ ከሆነ ሽርጥ አድርገው።” አቡሁረይራ ባስተላለፉት ሐዲስ ደግሞ  እንዲህ ብለዋል፦

“ትከሻው ላይ አንዳች ነገር ሳይኖር በአንድ ልብስ ብቻ አይስገድ።”

ከነዚህ ሐዲሶች የምንረዳው ነገር ቢኖር፤ አንድ ሰው ሰላት ውስጥ ሳለ መሰተር እንዳለበት ነው። ዐብዱል በር አንድ ሰው ሐፍረቱን መሸፈን እየቻለ ሳይሸፍን ከሰገደ ሰላቱ ተቀባይነት እንደሌለው የዑለማዎችን ስምምነት አስፍረዋል።

ይህን በማስመልከት ዑለማዎች ሀፍረት ገላን ለሦስት ይከፍላሉ፦ እነሱም፤ ቀለል ያለ፣መካከለኛ እና  ከባድ በማለት።

ከበድ ያለው ሀፍረት፤ ጨዋ የሆነች (ባሪያ ያልሆነች)  እና ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ሴት ከፊቷ  በስተቀር ሙሉ አካሏ ሰላት ውስጥ ሀፍረት ነው ይላሉ። መዳፎቿን እና እግሮቿን አስመልክቶ ሀፍረት ነው? ወይስ አይደልም? በሚል ዑለማዎች መካከል ኺላፍ አለ። ቀለል ያለው ሐፍረት ደግሞ ከሰባት እስከ አስር ዓመት ያለ ወንድ ልጅ ሐፍረት ሲሆን የርሱ ሀፍረት ከፊትም ሆነ ከኋላው ያለው ሀፍረት እንዲሁም ታፋውን መሸፈን ግዴታ አይሆንበትም። ምክንያቱም ገና ልጅ ነውና። መካከለኛ ሀፍረት የሚባለው ደግሞ ከነዚህ ውጭ ያለው ሀፍረት ነው። ከእንምብርት እስከ ጉልበት ያለውን ክፍል መሸፈን ግዴታ ነው ብለዋል። ይህ ብይን ከአስር አመት በላይ የሆነ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድን፣ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰችንም ሴት ሆነ ባሪያ የሆነች እናትን ያካትታል። ይህ ከመሆኑ ጋር ማንኛውም ሰው ወደ ሰላት ሲገባ ጌጡንና የክት ልብሱን መልበስ ይጠበቅበታል። ሆኖም እንበልና ሀፍረቱን ጨምሮ የሚሸፍንበት ልብስ ላይ ቀዳዳ ቢኖር በዚህ ጊዜ ይህን ልብስ ለብሶ የሚሰግደው  ሰላት ተቀባይነት አለው? ወይስ የለውም? የሚለው ጉዳይ ለውይይት ሊቀርብ ይገባል። በመቀጠልም አንዲት ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ሴት በዙሪያዋ ባዕድ የሆኑ ወንዶች ካሉ ሰላት ላይም ብትሆን ፊቷን መሸፈን ግዴታ ይሆንባታል። ምክንያቱም ሴት ልጅ ለባዕድ ወንዶች ፊቷን መግለጥ አይፈቀድላትምና።




Share

ወቅታዊ